በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሴት ተማሪዎችን ለማብቃት የኢንተርኔት ማዕከል ተሰርቶላቸዋል፡፡ 

0
199

አፍሪካ ኤድስ ኢኒሼቲቭ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ለሴት ተማሪዎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ሰርቶ የኢንተርኔት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ ማዕከሉን በማስመረቅ ክፍት አድርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና በማዕከሉ ምርቃት ወቅት እንደተናገሩት ዩ ኤን ኤፍ ፒ ኤ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ከአፍሪካ ኤድስ ኢኒሼቲቭ ጋር በጋራ በመሆን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለማብቃት እየተገበራቸው ያለውን ፕሮግራሞች አደንቃለው ብለዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ በንግግራቸው በተለይ ለሴት ተማሪዎቻችን እንደዚህ አይነቱ እድል መሠጠቱ ሴቶች እኩል ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ በቀጣይ ብቁና ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡

በካሪኩለምና ዲፓርትመንት ኢንስትራክሽን መምህርና የአፍሪካ ኤድስ ኢኒሼቲቭ ኮንሶልታንት የሆኑት አሶሼትድ ፕሮፌሰር መሰረት አሰፋ ለጣቢያችን እንደተናገሩት አካል ጉዳተኞች ፎቅ ወጥተው ወርደው ሊጠቀሙ አይችሉም  ስለዚህ እነዚህን ኮምፒውተሮች ከዶርማቸው በአጭር ርቀት እንዲያገኙ በማድረግ ችግሮቻቸው እንዲቀረፍ ታስቦ እንደተደረገ ነግረውናል፡፡

የአፍሪካ ኤድስ ኤኒሼቲቭ የፋይናንስና አስተዳደር ሀላፊ ወ/ሮ መንበረ አብረሃም ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ከዚህ በፊት አፍሪካን ኤድስ ኢኒሼቲቭና ዩ ኤን ኤፍ ፒ ኤ በጋራ በመሆን ከዚህ በፊትም ለአካል ጉዳተኞች 42 ኮምፒውተሮችን እንዲሁም 50 ኮምፒውተሮችን ለሴቶች በማቅረብ ወደ ማዕከል በመምጣት አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

አሁንም እንዲሁ ተጨማሪ 40 ኮምፒተሮችን የያዘ ማዕከል ለሴቶች አገልግሎት እንዲሰጡ በማስመረቅ ክፍት ማድረግ ተችሏል ይላሉ፡፡

ማዕከላቱ ለሴት ተማሪዎች የሚቀርቡበት ዋነኛ ምክኒያት ለማጥናት ሲሉ ከግቢው ርቀው በመሄድ ፆታዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው እንዲሁም ለኢንተርኔት ክፍያ የሚያወጡትን ወጪ ለመቀነስ ነውም ብላናለች፡፡

ዜናውን የፃፈው ደረሰ አማረ ነው፡፡

የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here