ብሄራዊና ክልላዊ ፈተናዎችን ለማሳካት የሚያግዝ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ዝግጅት እየተደረገ ነው—ትምህርት ሚኒስቴር

ብሄራዊና ክልላዊ ፈተናዎችን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የሚያግዝ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ በልዩ ጥንቃቄ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ አስታወቁ፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በብሄራዊና ክልላዊ ፈተናዎች አሰጣጥ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

ሚኒስትሩ በመድረኩ እንደገለጹት በተያዘው ዓመት በሀገሪቱ አንድ ሚሊዮን ሁለት ሺህ የአስረኛ ክፍል እና 322 ሺህ 12ኛ ክፍል ተፈታኞች ለፈተና ተዘጋጅተዋል

የዘንድሮው ብሄራዊ ፈተና ሀገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር በልዩ ጥንቃቄ እንዲፈጸም ትኩረት ተሰጥቷል።

በፈተናው ወቅት ችግር እንዳይከሰትና ሂደቱን በስኬት ለመፈጸም ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በፌዴራል ደረጃ ፈተናው እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት ደረጃ ተዘጋጅቶ ለስርጭት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ያመለከቱት ሚኒስትሩ ተጓጉዞ በየመፈተኛ ጣቢያዎች እስኪ ደርስ ድረስ በየደረጃው ያለው አመራር በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ፈተናውም በፌዴራል መረጃና ደህንነት፣በፌዴራል ፖሊስና ሌሎች ባላድርሻ አካላት አማካኝነት ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በ27 የደህንነት ካሜራዎች ታጅቦ ለስርጭት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ክልላዊና ሀገራዊ ብሄራዊ ፈተናዎች ከሰኔ 3 እስከ 14 /2011 ዓ.ም እንደሚሰጥ ጠቁመው የዘንድሮው ፈተና በተወሰነ መልኩ ሊራዘም የቻለው የሙስሊሞችን “የዒድ” በዓል ከግምት በማስገባት እንደሆነም አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው በክልሉ ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለማስኬድ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የብሄራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ሳይሆኑ የመላው ህብረተሰቡን ትብብር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ በበኩላቸው በክልሉ 804 ሺህ የ8ኛ ፣ 10ኛ እና የ12 ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ካምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ከ84 ሺህ በላይ ጭማሪ አሳይቷል። እንደ ክልል ፈተናውን በሰላም ለማጠናቀቅ ከ30 ሺህ በላይ ግብረሃይል መዘጋጀቱን አመልክተው ለሁሉም የፈተና ደረጃዎች ከአምስት ሺህ በላይ የመፈተኛ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ፈተናዎች ተጀምረው እስኪ ጠናቀቁ ድረስ የክልሉ የጸጥታ ኃይል በየደረጃው አደረጃጀት ፈጥሮ በትኩረት ለመስራት መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ናቸው።

የጸጥታ ኃይሉ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ በትብብር መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ የክልልና የፌዴራል የዘርፉ ስራ ኃላፊዎች ፣ የጸጥታ እና ሌሎችም አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *