300 ኢትዮጵያዊያን በኮሌራ ወረሽኝ መያዛቸውን ተገለጸ

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደገለጸው ወረሽኙ በትግራይ፣ በአዲስ አበባ፣በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቷል።

ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በማስከትል በሰውነት ውስጥ የሚገኝን ፈሳሽ አሟጦ በማስወጣት አቅምን በማዳክም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል ተከስቶ ከነበረው ወረርሽኝ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በጭሮና ኦዳ ቡልቱ ወረዳዎች እንዲሁም በበዴሳ ከተማ 115 ሰዎች፣ በትግራይ ክልል በምስራቃዊ ዞን በክልተ አውላሎ ወረዳ 8 ሰዎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ በአቃቂና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች 5 ሰዎች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው ህክምና እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡

የበሽታውን መንስኤ ለማረጋገጥ ከታካሚዎች ከተወሰዱ ናሙናዎች ላይ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ወረርሽኙን ያስከተለው ቪብሮ ኮሌራ የተሰኘ ባክቴሪያ መሆኑን እንዳረጋገጠ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ወረዳዎች የፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን በቦታው ተሰማርቶ ለዚህ አገልግሎት ብቻ ተብሎ በተቋቋሙ ጊዚያዊ የህክምና ማዕከላት ምላሽ እየተሰጠ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል የሚኖርባቸውና አገልግሎት የሚያገኙባቸው እንደ ስደተኞች መጠለያ፣የሃይማኖት ስፍራዎች፣ ህዝባዊ በዓላት በሚከበሩባቸው አካባቢዎች ወረርሽኙ በቀላሉ ሊከሰትና ሊሰራጭ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም አስታውቋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕብረተሰቡ ወረሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ እንዲሆንና ምግብን በሚገባ አብስሎ በመመገብ ከዝንቦችና ከሌሎች ነፍሳት ንክኪ በመጠበቅ ራሱንና ቤተሰቡን ከተላላፊ በሽታዎች እንዲከላከል ኢንስቲትዩት አሳስቧል።

ዘገባው ሄኖክ ወ/ገብርኤል ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *