ከ10 ዓመታት በላይ የፈጀው የድሬደዋ ሪፈራል ሆስፒታል በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገለፀ

በድሬደዋ ከተማ ኢንዱስትሪ አካባቢ በመገንባት ላይ የሚገኘው ሪፈራል ሆስፒታል በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር እየተተገበሩ ካሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ይህ ሪፈራል ሆስፒታል አንዱ ሲሆን በከተማው ማህበረሰብ መዋጮ የሚሰራ በመሆኑ የግንባታው መጓተት ቅሬታዎችን ሲያስነሳ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ም/ል ሀላፊ የሆኑትን አቶ የሱፍ ሰኢድ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ፤ ኮንትራክተሩ ችግር ገጥሞት ስለነበር የዲዛይን ማሻሻል ሂደቱ ፕሮጀክቱ ለመጓተቱ ምክኒያቶች ዋነኞቹ ነበሩ ብለዋል፡፡

አቶ የሱፍ እንዳሉት ዲዛይኑ በቀረበበት ወቅት የውጭ ምንዛሬው እንዳሁኑ ያልጨመረበት ሁኔታ ነበር ፤ በዚህም 2 መቶ ሚሊየን ብር ይጨርሳል ተብሎ ቢታቀድም ፤ እየጨመረ በመጣው የውጭ ምንዛሬ ምክንያት ፕሮጀክቱ ላይ ከእቅዱ በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩና ጤና ቢሮው ፕሮጀክቱ በዚህ ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት ላይ እንዲውል አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርጉ ሀላፊው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልፀዋል፡፡

ሪፈራል ሆስፒታሉ በድሬደዋና አካባቢዋ ያሉ እንዲሁም ለኦሮሚያና ሱማሌ ክልል ህዝቦችን ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት እንደሆነ ሀላፊው አቶ የሱፍ ሰኢድ ለጣቢያው አሳውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በድሬደዋ ኢንደስትሪ መንደር አቅራቢያ በመሰራቱ ለጅቡቲ ዜጎችም አገልግሎት እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡

ሆስፒታሉ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ሲገባ ለ5 መቶ ሺህ ህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተገነባ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ባልደረባችን ደረሰ አማረ እንደዘገበው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *