የኢትዮ-ጣልያን ቢዝነስ ጉባኤ ሊካሄድ ነው

ከ50 በላይ የጣሊያን ኩባኒያዎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ አቻዎቻቸው ጋር የሚገናኙበት የኢትዮ-ጣልያን ቢዝነስ ጉባኤ ሊካሄድ ነው።

ጉባኤው ከሰኔ 12 እስከ 13 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን ከ50 በላይ የጣሊያን ኩባኒያዎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ አቻዎቻቸው ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

የቢዝነስ ፎረሙ የኢትዮጵያ መንግስት ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚያደርገውን ማበረቻቻ ለመጠቀም እንዲሁም የጣሊያን መንግስትም እንዲሁ ኢትዮጵያን በመሰሉ ሌሎች ሀገራት መዋለ ንዋይ ለሚያፈሱ የጣሊያን ኩባንያዎች የሚያቀርበውን የፋይናንስ ድጋፍ እና የባንክ ድጋፍ ለመጠቀም ያለመ ነው፡፡

በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግኑኝነት ስኬቶችን የሚያወሳና ለወደፊትም አዲስ የትስስር አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ ነው ተብሏል፡፡

በጉባኤው በመሰረተ ልማት በጨርቃ ጨርቅ በቆዳና በግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ላያ የተሰማሩ ባለሀብቶችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

ፎረሙ የሚካሄደዉም በጥቅምት ወር የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጣሊያን ጉብኝት እንዲሁም የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ በጥር ወር ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ነው፡፡

የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግኑኝነት ባለፈው አመት 292 ሚሊየን መድረሱ ተገልጧል፡፡

ባልደረባችን ሄኖክ ወ/ገብርኤል እንደዘገበው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *