የቀድሞው የግብፅ ፕሬዝዳንት ሞትን ተከትሎ በግብጽ የጸጥታ ስጋት ተፈጥሯል

በሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ ተማረው ወደ ታህሬር አደባባይ በወጡ ግብጻዊያን ግፊት ነበር ወደ መንበረ ስልጣን የመጡት።

ከ6 ዓመት በፊት የግብጽ ፕሬዘዳነትነትን የተቆናጠጡት መሃመድ ሙርሲ በመጡበት ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ ስልጣናቸውን ቀምቷቸዋል።

መሃመድ ሙርሲ በምርጫ ስልጣን እንዳገኙ ቢነገርም በአገሬው አነጋገር ከግብጽ ታሪካዊ ጠላት ከሆኑት ቱርክ፣ኳታርና ሌሎች ግራ ዘመም ፖለቲካ ከሚከተሉ አገራት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ፈጥረዋል በሚል ነበር አብዮት የተነሳባቸው።

የሙስሊም ወንድማመቾች ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት መሃመድ ሙርሲ የአሁኑ የግብጽ ፕሬዘዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ወደ ስልጣን ከወጡበት ጊዜ አነስቶ በእስር ላይ ቆይተዋል።
በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም በመሃመድ ሙርሲና ቤተሰቦቻቸው ላይ ወከባዎችንና የሰብአዊ መብት መብት ጥሰቶችን ፈጽሞባቸዋል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ትናንት በካይሮ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ ድንገት ራሳቸውን ስተው ከወደቁ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

የሙርሲ ሥርዓተ-ቀብርም በከፍተኛ የጸጥታ አስከባሪዎች አጀብ ዛሬ ረፋድ ተፈጽሟል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቤተሰቦች በካይሮ ከተማ የቶራ እስር ቤት ውስጥ በሚገኝ መስጊድ የተደረገውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እና ሥርዓተ ቀብራቸውን ታድመዋል።

የመሐመድ ሙርሲ ልጅ አሕመድ እንደተናገሩት የአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሻርቂያ ግዛት በሚገኘው የትውልድ መንደራቸው በሚገኝ የቤተሰቦቻቸው የመቃብር ሥፍራ እንዳያርፉ ተከልክለዋል።

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው ደግሞ ጋዜጠኞች የቀብር ሥነ-ሥርዓቱን እንዳይከታተሉ ፎቶ ግራፍም እንዳያነሱ፣ ወደ ሙርሲ የትውልድ ከተማ እንዳይጓዙም የጸጥታ አስከባሪዎች ክልከላ አድርገዋል።

የቀድሞው የግብጽ ፕሬዘዳንት መሃመድ ሙርሲ “የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የግብጽን ታሪካዊ የውሃ ድርሻ የሚጎዳ ነው ታሪካዊ የውሃ ድርሻችንንም ለማስከበር እስከ ደም ጠብታ መስዋዕትነት እንከፍላለን” የሚለው ንግግራቸውን ብዙ ኢትዮጵያዊያን አይዘነጉትም።

ትርጉም በሳሙኤል አባተ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *