በኢትዮጵያ የወባና ኩፍኝ በሽታዎች ወረሽኝ መከሰቱ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንደገለጸው በኢትዮጵያ የወባ በሽታ በድጋሚ ተከስቷል።

የወባ በሽታ በተለያዩ ክልሎች የታየ ሲሆን በተለይም በደቡብ ክልል በወረሽኝ መልክ መከሰቱን አስታውቋል፡፡

በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን በ 6 ወረዳዎች በተለይም ዳሞት ጋሌ፣ በቦሌ ሶሴሬ፣ በቦሎሶ ቦምቤ፣ ኪነዶ ኮይሻ፣ ዳሞቴ ሶሬ እና ዳጉና ፉነጎ ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ የተከሰተባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

ከደቡብ ክልል በተጨማሪም በአማራ ክልል በባህርዳር ዙሪያና ደራ ወረዳዎች መከሰቱን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ የትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ የታቆሩ ውሃዎችን በማፍሰስ እንዲሁም የአልጋ አጎበር በመጠቀም እራሱን ከወባ ትንኝ ንክሻ እንዲከላከል አሳስቧል፡፡

በተያያዘ ዜና የኩፍኝ በሽታ በአፋር ክልል በአሳይታ ወረዳ የተከሰተ ሲሆን በወረርሽኙ 256 ሰዎች መያዛቸው ታውቋል፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከልም ክትባት በወረዳው እየተሰጠ ሲሆን 26 ህሙማን በአሳይታ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛልም ተብሏል፡፡

ይህ በንዲህ እንዳለ የጊኒዎርም በሽታ ደግሞ በጋምቤላ ክልል በጎግ ወረዳ በ4 ዝንጅሮዎች ላይ በመገኘቱ ኢኒስቲትዩቱ ከእንስሳት ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጾ የአከባቢው ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡

ዘገባው የባልደረባችን ሄኖክ ወ/ገብርኤል ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *