ኮሎምቢያ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ልትከፍት ነው

ኮሎምቢያ በአፍሪካ 7ኛ የሚሆነውን ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ ለመክፈት ዝግጅት እያደረገች መሆኗን አስታውቃለች።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የኤዥያ እና የባለ-ብዙ ወገን ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ ከኮሎምቢያ አቻቸው አልፌርዶ ራሞስ ጎንዛሌዝ ጋር በሁለትዮሽና ኤምባሲውን ለመክፈት በሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ዙሪያ ዛሬ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ማህሌት በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሁለቱ አገራት የቆዬ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር አላቸው።

የአፍሪካ ህብረት፣ የመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የበርካታ አገራት ኤምባሲዎችና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ ኮሎምቢያ ኤምባሲዋን ለመክፈት ማቀዷ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሌሎች የሚመለከታቸው አካለት ጋር በመሆን ለኤምባሲው በአፋጣኝ መከፈት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ለዳይሬክተሩ ገልጸውላቸዋል።

በኮሎምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ፣ ኤዥያ እና ኦሽኒያ ዳይሬክተር አልፌርዶ ራሞስ ጎንዛሌዝ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሰፊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባትና አገር በመሆኗ መንግስታቸው ኤምባሲ ለመክፍት መወሰኑን ተናግረዋል።

የኮሎምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ እንደሚመጡና የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ለማድረግ እንደሚፈልጉም ዳይሬተሩ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከ110 በላይ አገራት ኢምባሲዎቻቸውን ከፍተው የዲፕሎማሲ ስራዎቻቸውን በማቀላጠፍ ላይ ይገኛሉ።

መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *