በአዲስ አበባ ከሰኔ 30 በኋላ የሰሌዳ ቁጥር ሳይኖራቸው ሲንቀሳቀሱ የሚገኙ የሞተር ሳይክሎች እንደሚወረሱ ተገለጸ

ከሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ የሞተር ሳይክሎች ከተገኙ እንደሚወረሱ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።

የከተማዋ አስተዳደር ሞተር ሳይክል ተሽከርካሪ እና የጭነት መኪና በአዲስ አበባ ከተማ ያላቸውን እቅስቃሴ የተመለከተውን አዲስ መመሪያ ይፋ አድርጓል።

ከሰኔ 30 በኋላ ከየትኛውም ክልል የሚመጡ የሞተር ተሸከርካሪ በአዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫ እንዳይገቡ ይደረጋል ተብሏል።

በከተማዋ ለመንቀሳቀስ የሚፈቀድላቸው የሞተር ሳይክል ተሽከርካሪ የመከላከያ ፣ የትራፊክ ፍሰት ተቆጣጣሪ ፣ ነዳጅ የሚያመላልሱ እና ሌሎች ፍቃድ ያገኙ ተቋማት ተሸከርከሪዎች ብቻ በማንኛውም ጊዜ በከተማዋ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ የአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ ገልጸዋል፡፡

ስራን ለማፍጠን ሲባል በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሞተረኞች በማህበር ተደራጅተው የመስራት ዕድል ይኖራቸዋልም ብለዋል ዶ/ር ሰለሞን፡፡

ድርጅት ያለው ማንኛውም የድርጅቱን መለያ አርማ የለበሰ ሞተረኛ እና ሞተሩም በተመሳሳይ የድርጁቱ አርማ ያለው ከሆነ ፍቃድ ወስዶ ማሽከርከር ይቻላልም ብለዋል ሀላፈው፡፡

ማንኛውም የጭነት እንቅስቃሴ ከ 2 ነጥብ 5 ቶን እስከ 3 ነጥብ 5 ቶን ቀላል የጭነት ተሸከርካሪ እና ከ 3 ነጥብ 5 ቶን በላይ የመጫን አቅም ያላቸው ተሽከርካሪዎች በቀን መንቀሳቀስ አይችሉም ተብሏል፡፡

ማንኛውም ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ከጠዋቱ 12፡30 እስከ ምሽት 2 ሰዓት አዲስ አባባ ውስጥ መጫን እና ማውረድ እንዲሁም መቆም አይችሉም፡፡

ማንኛውም ቀላል የጭነት ተሽከርካሪ ከጠዋቱ 4፡00 እስከ ከሰዓት 10 ሰዓት በአዲስ አባባ መንቀሳቀስ ይፈቀድላቸዋል፡፡

ማሽነሪ፣ የውሃ ስራ ፣ አትክልት ውሃ የሚያጠጣ ተሸከርካሪ በቀን መንቀሳቀስ እንዳማይችሉም ተብሏል፡፡

መመሪያው ዝግ አይደለም በመደበኛ ፍቃድ 500 ብር በልዩ ፍቃድ 1 ሺህ ብር በቀን ክፍያ ከፍለው አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡

ዘገባው የዳንኤል መላኩ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *