በሶማሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጦር ከአሜሪካ አቻቸው ጋር ወታደራዊ ልምምድ ሊያደርጉ ነው

ወታደራዊ ልምምዱ የአሜሪካ መከላከያ አባላት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ጋር በጥምረት እንደሚያካሂዱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ አስታውቋል።

ልምምዱ የፊታችን ሰኞ የሚጀመር ሲሆን ለ17 ቀናት ይካሄዳል ተብሏል።

ልምምዱ በሶማሊያ በተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) አባላትን አቅም ማሳደግ ላይ ያተኮረ ሲሆን ወደ 1 ሺህ 100 የሚጠጉ ወታደራዊና የመንግስት ሃላፊዎች ይሳተፉበታል።

በልምምዱ ላይ ከብራዚል፣ ብሩንዲ፣ ካናዳ፣ ጂቡቲ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኬንያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ እና ከእንግሊዝ የተውጣጡ ወታደሮች ይሳተፋሉ።

በተጨማሪም እንደ አፍሪካ ህብረትና እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት፣ የአሜሪካ የሰላም ተቋምና ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር የተውጣጡ ባለሙያዎችም እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

ልምምዱ የመከላከያ አባላትን ዝግጁነትና አቅም በማሳደግ በሶማሊያና አካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተጀመረውን ጥረት ያግዛል ተብሏል።

በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስቱ የአገሪቱን ደህንነት ማስጠበቅ ባለመቻሉ ተጨማሪ ወታደር እንዲመጣለት በጠየቀው መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ሩዋንዳ፣ዩጋንዳ፣ብሩንዲና ጅቡቲ የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ መቋዲሾ በመላክ ጽንፈኛው አልሻባብ የሽብር ቡድንን በመዋጋት ላይ ይገኛሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *