ታይዋን – የአሜሪካና ጋሻ ጃግሬዎቿ መጫወቻ ካርድ

ታይዋን – የአሜሪካና ጋሻ ጃግሬዎቿ መጫወቻ ካርድ 

ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቻይናና አሜሪካ በጎሪጥ የሚተያዩበት ጊዜ ይመስላል፡፡

ሁለቱ የዓለማችን ባለ ግዙፍ የኢኮኖሚ ሀገራት አሜሪካና ቻይና ግብግባቸው አሁንም የሚቆም አይመስልም፡፡

በቅርቡ በመካከላቸው የተፈጠረው የንግድ ጦርነት መቋጫ ሳያገኝ ታይዋን የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትለውን ቻይናን ያስቆጣ ውሳኔ አሜሪካ አሳልፋለች፡፡

አሜሪካ ያበጠ ይፈንዳ በማለት ለታይዋን የ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ነው ውሳኔ ያሳለፈችው፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለታይዋን እንደ አስፈላጊነቱ ተግባራዊ የሚደረግ የ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል ማፅደቁን አሳውቀዋል፡፡

የጦር መሳሪያ ሽያጩ ዋሽንግተን ኤም 1 ኤ2 የተሰኘ ታንክን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ የጦር መሳሪያዎችን የሚያካትት መሆኑንም አሳውቃለች፡፡

በቅርቡ አሜሪካ ለታይዋን 330 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ለመፈፀም መወሷናን ተከትሎ ቻይና አሜሪካ ውሳኔውን በድጋሜ እንድታጤነው ማስጠንቀቋም የሚታወስ ነው፡፡

አሜሪካ ከታይዋን ጋር በየትኛውም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ መስክ ቀጥተኛ ግንኙነት የላትም፡፡

ነገር ግን በወታደራዊ መስኮች አብረው መስራት ከጀመሩ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የአሜሪካው ፕዝዳንት ዶንልድ ትራምፕ የሀገራቸው ባለስልጣናት ወደ ታይዋን ጉዞ እንዲያደርጉና ከታይዋን አቻዎቻቸው ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ የሚፈቅድ ህግ ማጽደቃቸው ሌላው ቻይናን በእጅጉ ያስቆጣ ተግባር ነው፡፡

የታይዋን አሁነኛ እንቅስቃሴ ከአሜሪካ ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት ቤጂንግና ዋሽንግተን የሚፋጠጡበትን ሌላው መስክ  ሆኗል፡፡

ቻይናና አሜሪካ በደቡባዊ የባህር ዳርቻ የገቡበትን እሰጥ አገባ መቋጫ ሳያገኝ በታይዋን ጉዳይ ሌላ ውጥረት መግባታቸው ሁለቱ ሀገሮች ከጀመሩት የንግድ ጦርነት የበለጠ የዓለምን ትኩረት ስቧል፡፡

ይሄ ሁኔታ ሁለቱን ሀገሮች ወዴት ያመራቸው ይሆን በሚባልበት በአሁኑ ወቅት ታይዋን ከዋሽንግተን ጋር የጦር ልምምድ ለማድረግ ጊዜው አልደርስ ብሎኛል ማለቷና አሜሪካም ለታይዋን በሯን ክፍት ማድረጓ ነገሩን ይበልጥ ያከረዋል የሚሉ ሰዎች እንዲበራከቱ አድርጎታል፡፡ 

ሲ ኤን ኤን እንደዘገበው የታይዋን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ግዥ ውሳኔ ቻይና ወታደራዊ አቅሟን እያዘመነች በመምጣቷና ቀጣናውን ለመቆጣጠር ያላትን ፍላጎት ተከትሎ ነው ሲል አስፍራል፡፡

ቤጂንግ የምታደርገው ወታደራዊ እሽቅድምድም መነሻ ምክኒያት በረዥም ጊዜ ታይዋንን መልሶ የማዋሃድ ከፍተኛ ፍላጎት ነው ሲል የአሜሪካ
ደህንነት አጀንሲ ዘግባል፡፡

ታይዋን በበኩሏ የጦር መሳሪያ ግዥው የእግረኛና የአየር ወታደራዊ አቅማችንን በማሳደግ  የወታደራዊ ስነ ልቦናን በመገንባት እንዲሁም ለአለም ማህበረሰብ አሜሪካ የታይዋን ዋና አጋር መሆኗን ለማሳየት ነው ብላለች፡፡

የታይዋን መከላከያ ሚንስትር ቹንግ ቻይ አሁን የሚያጓጓን ነገር ቢኖር አሜሪካ በየሁለት ዓመቱ በምታካሂደው የሀዋይ የጦር ልምምድ መሳተፍ ነው ብለዋል፡፡

ቻይና ይህን አባባል አትቀበለውም ምክንያቱም ታይዋን ራሷን ችላ ከሌላው ዓለም ጋር ይፋዊ ግንኙነት መመስረት አትችልም የሚል ጽኑ አቋም ስላላት ነው፡፡

በተለይ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ እሰጥ አገባ ሲገቡ ተስተውሏል፡፡

የቻይና የመከላከያ ሚኒስትር በበኩላቸው ቤጅንግ አሜሪካ ለታይዋን የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭና ወታደራዊ ግንኙነት በጥብቅ ትቃወማለች ብለዋል፡፡

የታይዋን ጉዳይ የቻይና የውስጥ ጉዳይ ነው ለቻይናዊያን ብሄራዊ ጥቅም የውጭ ጣልቃገብነትን አንፈቅድም ያሉት ደግሞ የቻይና መከላከያ ቃል አቀባይ ናቸው፡፡

ቃል አቀባዩ አክለው እንደተናገሩት እንደነዚህ አይነት አደገኛ እንቅስቃሴዎች ለአንዳቸውም ቢሆን አይጠቅምም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሽ ጂንፒንግ ታይዋን የቻይና አካል መሆኗን ታሪክም ህግም ይደግፈናል ስለሆነም ከአቋማችን አናፈግፍግም ብለዋል፡፡

ሺ ይህን ያሉት ቻይና ከታይዋን ጋር የምታደርገውን ጦርነት አቁማ በሰላም የመዋሀድ ሀሳብ ያቀረበችበትን  ዓመት በምታከብርበት ወቅት ነው፡፡

አንዲት ጠንካራ ቻይና ሳይሆን ሁለት ቻይናዎች እንዲኖሩ የሚያሴሩትን ሁሉ አጥብቀን እንቃወማለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ ታይዋንን የቻይና አካል ለማድረግ ሁሉንም የእርምጃ አማራጮች እንወሰወዳለን ብለዋል፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው ነገሮች በሰላም የማይቋጩ ከሆነ የፕሬዝዳንት ሽ ጂንፒንግ አስተዳደር የመጨረሻ አማራጩ ታይዋንን በሀይል ማስመለስ ሊሆን ይችላል ሲል አትቷል፡፡

እስከዛሬ ታይዋን ራሷን ችላ ሀገር እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ሁሉ በማክሸፍ ብዙ ስኬቶችን አስመዝግበናል አሁንም ይህች ደሴት የቻይና አካል ስለመሆኗ የሚጠራጠር ካለ እሱ ተሳስቷል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ፡፡

የታይዋን ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ቻይና የ23 ሚሊዮን ህዝብ ፍላጎት እና በነፃነት የመኖር መብት ልታከብር ይገባል በማለት ቻይናን ወቅሰዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ግን ሰላማዊ ድርድር ውጤት ካላመጣ ጦርነት ወስጥ ለመግባት የምንገደድበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም የሚል ንግግር አድርገዋል፡፡

በተለይ በውስጥ ጉዳያችን እየገቡ ፖሊሲያችንን የሚፈታተን ድርጊት የሚፈፅሙ ወገኖች እጃቸውን መሰብሰብ አለባቸው ሲሉም ጠንከር ያለ የማስጠንቀቂያ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ከፈረንጆቹ 2010 ጀምሮ አሜሪካ ለታይዋን የ15 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳርያ ሽያጭ አድርጋለች በተቃራኒው ከቻይና ጋር ደግሞ ከፍተኛ የንግድ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡

ፕሬዘዳንት ትራምፕ በአሜሪካ ተቅደም ፖሊሲያቸው በተደጋጋሚ ቻይናን የሚያበሳጩ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን ቀጥለዋል።

ቻይና ከዓለም ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ስር ስር ማለቷን ያልወደዱት ፕሬዘዳንት ትራምፕና መንግስታቸው ቻይና በአፍሪካና በተቀረው ዓለም እያስመዘገበች ያለውን ዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ግስጋሴ ለመግታት ከፍተኛ ግብር ከመጣል አልፎ ከቻይና ጋር ጥሩ ወዳጅነት በመሰረቱ አገራትና በቻይና ግዙፍ ኩባንያዎች ላይ የተለያዩ ድብቅ ሴራዎችን እንደሚፈጽሙ የተለያዩ ትንታኔዎች በመሰጠት ላይ ናቸው።

የአሁኑ የሁለቱ አገራት ውዝግብ ወዴት ያመራ ይሆን የሚለው የብዙዎችን ትኩረት መሳቡን ቀጥሏል።

በሔኖከ ወ/ገብርኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *