የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለማስተላለፍ የወጣው መመሪያ የህግ ክፍተት አለበት ተባለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ያወጣው መመሪያ የህግ ክፍተት እንዳለበት የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አስታወቀ።

ጉባኤው እንዳስታወቀው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች እና ለልማት ተነሺዎች ለማስተላለፍ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2008 አንቀጽ 44 (ሐ) እና (ሠ) የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 40 ድንጋጌዎች የሚቃረን ነው።

መዝገቡ ወደ አጣሪ ጊባዔው ሊቀርብ የቻለው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 150818 ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በአንድ አመልካችና በተጠሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ መሀከል ሲካሄድ ከነበረው የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ጋር የተያያዘ ክርክርን ሲመለከት ቆይቶ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት በጉዳዩ ላይ ተፈፃሚነት ያለውን “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎችና ለልማት ተነሺዎች ለማስተላለፍ የወጣውን መመሪያ ቁጥር 1/2008 አንቀፅ 44” ሕገ መንግሥታዊነት እንዲመረመር በመላኩ ነው፡፡

የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች እና ለልማት ተነሺዎች ለማስተላለፍ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2008 አንቀጽ 44 (ሐ) እና (ሠ) የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 40 ድንጋጌዎች እና ሌሎች የሕገ መንግሥቱን መርሆዎች የሚቃረን መሆኑን አጣርቷል።


በዚህም ጉባኤው ባደረገው ማጣራት መመሪያው የህግ ክፍተት ያለበት በመሆኑ የውሳኔ ሀሳቡን ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲላክ መወሰኑን ገልጿል፡፡

ጉባዔውም የጉዳዩን ሕገ መንግሥታዊነት በመረመረበት ወቅት የጉዳዩን ክብደት በመረዳት ከከተማው አስተዳደር ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ኃላፊና ባለሙያ አስቀርቦ በጉዳዩና በድንጋጌዎቹ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ተቀብሏል።


በመመሪያው አንቀፅ 44 የቤት ዕድለኛ በሞተ ጊዜ ዕድሜያቸው 18 ዓመት የሞላቸው የሟች ልጆች በሟች ስም የወጣውን ዕጣ አይወርሱም በሚል የደነገገ በመሆኑና ይህ ደግሞ በሟች ወራሾች መካከል ልዩነት በመፍጠር ቤት የሌላቸው ግለሰቦች በውርስ መልክ የሚያገኙትን የቤት ባለቤትነት መብት የሚሸረራርፍ በመሆኑ ጉባዔው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ስር የተደነገገውን የዜጎች የንብረት መብት የሚያጣብብ እና ከሌሎችም የሕገ መንግሥቱ መርሆዎች ጋር የሚጋጭ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።

በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2008 አንቀጽ 44 (ሐ) እና (ሠ) ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 እና ከሌሎችም የሕገ መንግሥቱ መርሆዎች ጋር ስለሚቃረን የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ለመጨረሻ ውሳኔ ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ልኮታል።

ዘገባው የሳሙኤል አባተ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *