እውን በድሬዳዋ ከተማ መፈንቅለ ከንቲባ ተካሂዷል?

ከሰሞኑ በድሬደዋ ተካሄደ የተባለው ከንቲባው አቶ መሃዲ ጊሬ በፈረንሳይ ሃገር ለስራ ባቀኑበት ወቅት እንደነበርም ተነግሯል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤምም በህገ-ወጥ መንገድ ስልጣንን ለመውሰድ ተደረገ የተባለውን ሙከራ አጣርቷል፡፡

የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ እስቂያስ ታፈሰ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ሚዲያው በፈለገው መንገድ እየተረጎመ የሚሄድበት አግባብ ቢኖርም በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ላይ የተሞከረ ምንም ነገር የለም ብለዋል፡፡

በወቅቱ ከንቲባው ለስራ ውጭ ሀገር ስለነበሩ ምክትላቸው እሳቸው በሌሉበት ሁኔታ ተክተው የመስራት ሀላፊነት ስላለባቸው በዛ መንገድ በከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ላይ አጠቃላይ ግምገማ መደረግ እንዳለበት ተስማምተን ወደ ውይይት ገብተናል ብለዋል፡፡

የድሬደዋ ከንቲባ አቶ መሃዲ ጊሬ ሀገር ውስጥ በሌሉበት ሁኔታ ካቢኔው ግምገማ ማካሄዱ ከንቲባውን በሌሉበት ከስልጣን ለማውረድ የተደረገ ሙከራ ነው ልንለው እንችላለን..በወቅቱስ በካቢኔው መካከል አለመስማማት ተፈጥሮ ነበር ወይ ስንል ጠይቀናል፡፡

ሀላፊው እንዳሉት ምንም አለመግባባት አልተፈጠረም፡፡ በሂደቱም ከንቲባውን በተመለከተ ምንም ውሳኔ ላይ አልደረስንም፡፡ ይሁን እንጂ ከንቲባው ነገሩን ውጭ ሀገር በነበሩበት ወቅት ነገሩን በተረጎሙበት ምክኒያት ወደ መረጃ መዛባት ውስጥ ገብተናል በማለት ለጣቢያው ተናግረዋል፡፡

አሁን ምክትል ከንቲባው የዋናውን ቦታ ተክተው እየሰሩ ነው ወይ ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ሀላፊው አቶ እስቅያስ ሁለቱም ከንቲባዎች እንደቀድሞው በስራቸው ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

በደረሰ አማረ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *