የጉምሩክ ኮሚሽን በ2011 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና የገንዘብ ኖቶች በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ገለፀ

የጉምሩክ ኮሚሽን በ2011 በጀት ዓመት ወደ ሀገር ሊገቡና ከሀገር ሊወጡ የነበሩ 1 ቢሊዮን 633 ሚሊዮን 598 ሺህ 338 ብር የሚገመት የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብሏል፡፡

ከዚህ ውስጥ 1 ቢሊዮን 298 ሚሊዮን 765 ሺህ 42 ብር የሚገመተው የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ሲሆን የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር 334 ሚሊዮን 833 ሺህ 296 ብር እንደሚገመት ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አሳውቋል፡፡

ኮሚሽኑ የኮንትሮባንድ መከላከል ስራውን ሳከናውን የነበረው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ባሉት 14 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቼ ነው ያለ ሲሆን የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በቁጥጥር ስር ከማዋል የነበራቸው ድርሻ አዲስ አበባ ኤርፖርት ፣ ሀዋሳ እና ጅግጅጋ ቅርንጫፎች ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል ብሏል፡፡

ወደ ሀገር ሲገቡ ከተያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ አዳዲስ አልባሳት፣ኤሌክትሮኒክስ እና ምግብና መጠጥ ነክ ከፍተኛ ድርሻ አላቸውም ተብሏል፡፡

ከሀገር ለማስወጣት ተሞክሮ በቁጥጥር ከዋሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች፣ አደንዛዥ ዕፅና ምግብ ነክ ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል፡፡

ከኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የወጪ ኮንትሮባንድን ከመቆጣጠር አንፃር ከፍተኛ መጠን ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በመያዝ አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ጅግጅጋ እና ሞያሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ እንደያዙም ተነግሯል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ሲያውል የህብረተሰቡ ተሳትፎ፣ የጉምሩክ ሰራተኞች እና በየደረጃው ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት እንደሆነ ገልጧል፡፡

ዘገባው የሔኖክ አሥራት ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *