የኢቦላ ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ልዩ ክትትል እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ

የዓለም ጤና ስጋት የሆነው ኢቦላ ቫይረስ በዴሞክራቲክ ኮንጎና ጎረቤት አገራት በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በቫይረሱ የተያዘ ሰው የመዳን ዕድሉ 50 በመቶ መሆኑን ይናገራል፡፡

በቶሎ ህክምና ያላገኘ የኢቦላ ተጠቂ ከ2 እስከ 21 ባሉት ቀናት ውስጥ የመሞት እድሉ ከፍተኛ እንደሆነም ያስረዳል፡፡

ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ልዩ ክትትል እያደረገ መሆኑን ያስታወቀው ኢንስቲትዩቱ በተለይም በቦሌ፣ባህርዳር፣ድሬዳዋና መቀሌ አውሮፕላን ጣቢያዎች በኩል በሚገቡ መንገደኞች ላይ ልዩ ክትትል እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

በየብስ ትራንስፖርት ወደ አገር ወስጥ በሚገቡ መንገደኞች ላይ ደግሞ በ21 የፍተኛ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ክትትል በመደረግ ላይ ነው ተብሏል።

ቫይረሱ ሲይዝ ከፍተኛ ትኩሳት፣ተቅማጥ፣የጡንቻ መገጣጠሚያ ህመም፣ የጉበት ህመም፣ደም መፍሰስ፣የኩላሊት መታወክ፣የጉሮሮ መቁሰል ያጋጥማል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በ 1976 በደቡብ ሱዳን እና በኮንጎ የተከሰተው ኢቦላ ቫይረስ 30 ጊዜ በወረርሽኝ መልክ ተቀስቅሶ ባለፉት 5 ዓመታት ወስጥ ብቻ ከ1870 በላይ ዜጎችን ገድሏል።

ዘገባው ሔኖክ ወ/ገብርኤል ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *