ቶጎ ሰላማዊ ሰልፎችን የሚከለክል አዲስ ህግ አወጣች

በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቶጎ እየታየ ያለውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ፓርላማው የተቃውሞ ትዕይንተ ህዝብ ላይ ተጨማሪ ገደብ የሚጥል ህግ አፅድቋል፡፡

መንግስት ህጉ ማስፈለጉ የሀገሪቷን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ነው ያለ ሲሆን ተቃዋሚዎች ግን እንደ አውሮፓውያኑ ከ1967 ጀምሮ የፕሬዝዳንትነቱ ስልጣን ከአንድ ቤተሰብ አለመውጣቱ ያስቆጣቸውን ተቃውሞ ሰልፈኞች ለማፈን ያቀደ ህግ ነው እያሉ ነው፡፡

በአዲሱ ህግ መሰረት በዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች ላይ፣የከተማ አደባባዮች ላይ፣እንዲሁም ከመንግስት መስርያ ቤት ህንፃ አቅራቢያ ምንም አይነት የተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ አይቻልም፡፡

ከጠዋቱ 5 ሰአት በፊትና ከምሽቱ 12 ሰአት በኋላም ተቃውሞ ሰልፎቹን ማካሄድ እንደማይቻል ህጉ ይደነግጋል፡፡

መንግስት የሽብርተኞች እንቅስቃሴ ስጋት ስለሆነበት ህጉን ለማውጣት እንደተገደደ ቢናገርም ከህዝቡ እየጨመረ የመጣውን ተቃውሞ ለማፈን እንደሆነ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተነገረ ነው፡፡

የተሸሻለው የቶጎ ህገ መንግስት አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙትን ፕሬዝዳንት ፋውሬ ግናሲንግቤ እንደ አውሮፓውያኑ እስከ 2030 በስልጣን እንዲቆዩ ይፈቅዳል፡፡

ይሄ ማለት የግናሲንግቤ ቤተሰብ ለ63 አመታት በስልጣን መቆየት እንዲችል ያደርገዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሔኖክ አስራት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *