ለ10 ሰዎች ሞትና ለበርካታ ዜጎች ጉዳት መንስኤ በሆነው በምእራብ ሀረርጌ ዞን ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ላይ የአመራሮች እጅ ነበረበት ተባለ

12 Aug by Ethio

ለ10 ሰዎች ሞትና ለበርካታ ዜጎች ጉዳት መንስኤ በሆነው በምእራብ ሀረርጌ ዞን ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ላይ የአመራሮች እጅ ነበረበት ተባለ

በቦርደዴ ወረዳ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እና የሰዎች ህይወት ህልፈት ላይ የአመሮች እጅ እንደነበረበት ሰምተናል፡፡

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ከወረዳው ሊቀመንበር ጀምሮ የተለያዩ አመራሮች፣ የቦርደዴ ወራዳ ወንጀል መከላከል ፖሊሶች ጭምር በድርጊቱ ተሳትፈው ነበር ብለዋል፡፡

በወረዳው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ያደረሱ እንዚህ አካላትን ጨምሮ 7 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ሰምተናል፡፡

የሀገር መከላከያ፣ፌደራል ፖሊስ እና የሀገር ሽማግሌዎች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመወያየት ወንጀለኞችን አሳልፈው እንዲሰጡ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ጥቃት አድራሾቹን ህብረተሰቡ አሳልፎ መስጠቱንም አቶ ጀይላን ነግረውናል፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ችግሩ የተከሰተበትን አካባቢ የማረጋጋት እና ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረቡን ስራ እያከናወነ ነው ሲሉም ለጣቢያችን አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ሀረርጌ ዞን ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ የታጠቁ ሀይሎች በወረዳዋ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ፈፀመው 10 ሰዎችን መግደላቸው የሚታወስ ነው፡፡

ዘገባው የሪፖርተራችን ትዕግስት ዘላለም ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *