ለ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህጻናት የልደት ማስረጃ ወረቀት በነጻ ሊሰጥ ነው

12 Aug by Ethio

ለ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህጻናት የልደት ማስረጃ ወረቀት በነጻ ሊሰጥ ነው

በሃገራችን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የተጀመረው ነሃሴ 30 2008 ዓ/ም ሲሆን እድሜያቸው ከ1 አመት በታች ከሆኑ ህጻናት ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በዚሁ ሂደት ተመዝግበዋል፡፡

ባሳለፍነው ቅዳሜ ሁለተኛው የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ስታቲስቲክስ ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል፡፡

በእለቱ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተገኙ ሲሆን ዘመናዊ አኗኗርን ለሚከተል ህዝብ ህጋዊ ምዝገባ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ለሰብአዊ መብቶች መከበር ግለሰባዊ ማንነት ህጋዊ ዋስትና ሊያገኝ ይገባልም ብለዋል ፕሬዘዳንቷ፡፡

የተባበሩት መንግስታት በ2030 የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መጠንን 100 ፐርሰንት ለማድረስ እየተሰራ ሲሆን በአፍሪካ ደግሞ በ2063 የልደት ምዝገባን 100 ፐርሰንት ፤የሞት ምዝገባን 85 ፐርሰንት ለማድረስ እቅድ ተይዟል፡፡

ይህን ለማሳካትም በሃገራችን ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገገባ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጧል፡፡

ለ2012 የትምህርት ዘመን በመላው የሃገሪቷ ክፍል የተማሪዎች ምዝገባ ሲካሄድ ፤ሁሉም ተማሪዎች የልደት ምስክር ወረቀት ይዘው እንዲቀርቡ ለማድረግ የፌዴራል ኢሚግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ሙሉ ወጪውን በመሸፈን የምስክር ወረቀቶችና የክብር መዝገብ ቅጾችን በማሳተም እንዲሰራጭ መደረጉ ተገልጧል፡፡

በዚህም 2.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት የልደት የምስክር ወረቀት እንደሚያገኙ የኢሚግሬሽን ዜግነትና እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል ተናግረዋል፡፡

የዜጎችን ህጋዊ መብቶች ለማስከበር፣ለአስተዳደራዊ ጉዳዮችና ለስታትስቲካዊ መረጃዎች በሚያገለግለው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ 1.1 ቢሊዮን የአለማችን ህዝቦች አለመካተታቸውን ከዝግጅቱ ሰምተናል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ግማሽ ቢሊዮን የሚሆኑት የኤዢያና አፍሪካ ሃገራት ዜጎች ናቸው፡፡

በሃገራችንም 65 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ህጋዊ ምዝገባ አላካሄደም፤በተለይም ህጻናትና ሴቶች ተብሏል፡፡

አባይነሽ ሽባባው እንደዘገበችው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *