ስቴፋኒ ፍራፓርት-‹‹በቴሌቪዥን የሚያዩኝ ልጃገረዶች /ሴቶች ሁሉ ነገር እንደሚቻል ያውቃሉ ››

አልቢትሯ ከፈረንሳይ ምርጥ ዳኞች አንዷ ናት ፡፡ ዛሬ በኢስታምቡል በሊቨርፑል እና ቼልሲ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ በመሃል ዳኝነት ትመራለች፡፡

 የሚጨበጨብላቸው ዳኞች ጥቂት ናቸው ፡፡ እነርሱን የሚያወድስ መልዕክት በስታዲየሞች መመልከት ብርቅ ነው ፡፡ ባለፈው ሚያዚያ የአሚዬ ደጋዎች ያደረጉት ብዙዎችን ያስገረመው ለዚያ ነው ፡፡ ስትራስቡርግን ካስተናገዱበት ጨዋታ ቀደም ብሎ የተለየ ነገር ፈጸሙ ፡፡በርግጥ አጋጣሚው ታሪካዊ ነበር ፡፡በፈረንሳይ ሊግ 1 በሴት የተዳኘ የመጀመሪያው ጨዋታ ነበር ፡፡አርቢትሯ ደግሞ ስቴፋኒ ፍራፓርት፡፡የባለሜዳው ቡድን ደጋፊዎች ከፍ አድርገው የያዙት ባነር ደግሞ ‹‹ወደ ስታድ ደ ላ ሊኮርን እንኳን በሰላም መጣሽ እመቤት ፍራፓርት ፡፡ረዥም ዕድሜ በእግር ኳስ ውስጥ ላሉ ሴቶች!›› የሚል ነበር፡፡ 

በኢስታምቡል የሱፐር ካፕ ፍጻሜን በመዳኘት አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ወደ ሜዳ ስትገባ የሊቨርፑል እና ቼልሲ ደጋፊዎች ተመሳሳይ አቀባበል ያደርጉላት ይሆናል ፡፡ በአውሮፓ መድረክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የወንዶች ጨዋታ በሴት ዳኞች ሲመራ ይህኛው ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል ፡፡ ፍራፓርትን በረዳትነት የሚያግዟት  የሃገሯ ልጅ ማኑኤላ ኒኮሎሲ እና አየርላንዳዊቷ ሚሼል ኦኒዬል ናቸው ፡፡ሶስቱ ከዚህ ቀደምም በጋራ ትልቅ ጨዋታ መርተዋል ፡፡ በዚሁ ዓመት በፈረንሳይ አስተናጋጅነት የተካሄደውን የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያ የመሩት እነርሱ ናቸው፡፡ ዛሬ ምሽት በቮዳፎን ፓርክ የሁሉም ሰው ዓይን እነርሱ ላይ እንደሚያነጣጥር ምንም ጥርጥር የለውም ፡፡

‹‹ጫናው የተለየ እንደሚሆን ይሰማኛል ፡፡ ሰዎች ጨዋታውን እንዴት ባለ ብቃት እንደምመራው ለመመልከት እንደሚጠብቁ አውቃለሁ ››ትላለች ፓሪስ አቅራቢያ በምትገኘው ቫል ዶይዝ ተወልዳ ያደገችው እና ተጨማሪ ጫናን የተላመደችው የ35 ዓመቷ አርቢትር ፡፡

በሊግ 1 በደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ የሚገኙት አሚዬ እና ስትራስበርግ ያደረጉት ጨዋታ ለወትሮው እምብዛም ትኩረት የሚሰጠው አልነበረም ፡፡ ጨዋታውን የምትመራው እርሷ እንደሆነች ከታወቀ በኋላ ግን መነጋገሪያ ሆነ ፡፡ እስከዚያች ዕለት ድረስ በአውሮፓ አምስቱ ቀዳሚዎቹ ሊጎች በሴት ዳኛ የተመራን ጨዋታ አስተናግዶ የሚያውቀው ቡንደስሊጋው ብቻ ነበር ፡፡ በ2017 ቢቢያና ስቴንሃውስ በቡንደስሊጋው ጨዋታ መምራቷ ይታወቃል ፡፡

በፕሪምየር ሊጉ ሲያን ማሲ-ኤሊስ በረዳት ዳኝነት ታገለግላለች ፡፡ በመሃል ዳኝነት ግን እስካሁን ዕድል ያገኘች ሴት የለችም ፡፡ የፈረንሳይ የእግር ኳስ ባለስልጣናትም ብዙ ጊዜ ወስዶባቸዋል ፡፡ፍራፓርት ባለፈው ሚያዚያ የወንዶቹን ጨዋታ  በመሃል ዳኝነት እንድትመራ ዕድሉ የተሰጣት በፈረንሳይ እግር ኳስ ለሴት ዳኞች ፋና ወጊ የነበረችው ኔሊ ቪዬኖ በሊግ 1  የመስመር ዳኛ ሆና ካገለገለች ከ23 ዓመት በኋላ ነው ፡፡

የአሚዬ እና ስትስቡርግ ጨዋታ ያለ እንከን ተጠናቀቀ፡፡ያ የሆነው ያለግብ በመጠናቀቁ ብቻ አልነበረም ፡፡የለ ኪፑ ጋዜጠኛ ዮሃን ሃውትቧ ስለጨዋታው በጻፈው ሪፖርት ‹‹እውነት ለመናገር እያንዳንዱን እንቅስቃሴዋን ተከታትለናል ፡፡የተመለከትነውን በሙ በማስታወሻችን አሰፍረናል ፡፡ሜዳውን የፈተሸችበት መንገድ፣ከረዳቶቿጋር ያሟሟቀችበትን መንገድ፣የአግድሞሽሩጫዎቿን ፣የተለመዱ መመዘኛዎችን ፣የመጀመሪያ ውሳኔዋን (በአራተኛው ደቂቃ ሴህሩ ጉራሲ የፈጸመውን ጥፋት ያስቆመችበት አጋጣሚ)እና ሌሎችም ፡፡ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስለ እርሷ ማሰብ ተውን ፡፡ እርሷን መመልከትም ሆነ መከታተልም አቆምን ›› ብሎላታል ፡፡ ይህን ጊዜ የቀየውን አባባል ማስታወስ ግድ ይላል ፡፡ ምርጦቹ ዳኞች ብዙም ልብ የማይባሉ ናቸው ፡፡ውሳኔዎቻቸው አጨቃጫቂዎች ስለማይሆኑ ተመልካቹ እነርሱን ረስቶ ኳሱ ላይ ብቻ ያተኩራል ፡፡

 ‹‹ሜዳ ላይ ከነበሩት 23 ተዋናዮች አብዛኞቹ ውሳኔዎች ትክክል የነበሩት የእርሷ ነበር ››ሲልም ሃውትቧ ይደመድማል ፡፡

“በዚያ መገኘት የሚያስችለኝ ክህሎት እና ችሎታ እንዳለኝ አሳይቻለሁ ›› ትላለች ከ23ቱ የሃገሪቱ ቀዳሚ ዳኞች ዝርዝር ውስት በመካተቷ በዚህ የውድድር ዘመን በቋሚነት የሊግ 1 ጨዋዎችን የምትመራው ፍራፓርት ፡፡ከወንዶቹ ጋር ተመሳሳይ የአካል ብቃት ፈተና አልፋ ዕሉን ያገኘችው ፍራፓርት ‹‹ዳኛዋ ሴት ናት ብለው ተጫዋቾቹ ፍጥነታቸውን አይቀንሱም››በማለት የሚጠብቃትን ጠንቅቃ እንደምታውቅ ማረጋገጫ ትሰጣለች፡፡

በፈረንሳይ ሁለተኛው እርከን  ከ2014 ጀምሮ ጨዋታዎችን ሰትዳኝ የሚውቋት በዕድገቷ አይገረሙም፡፡በሊግ 2 ምርጧ ዳኛ ነበረች፡፡ ብሏል የ US Orléans አማካይ Pierre Bouby ከወራት በፊት ስለ እርሷ ሲጠየቅ ፡፡“ድምጻ ዝቅ ያለ ነው ፡፡ ነገር ግን ግርማ ሞገስ ተላብሳለች፡፡ የምታስረዳህ ትክክለኞቹን ቃላት ተጠቅማ ነው ፡፡ ራሷን የትኩረት ማዕከል ለማድረግ አትሞክርም ፡፡ የምትጥረው ለጨዋታው የተሸለውን ነገር ለመስራ ነው፡፡

የሊሉ አሰልጣኝ ክርስቶፈር ጋላቲዬ ተመሳሳይ ምልከታ አላቸው ፡፡ ከፈረንሳይ ሚዲያዎች ጋር ባደረጉት ቆይታ  “ሲበዛ diplomaticነች ፡፡አሰልጣኝ ስትሆን እና ጫና ሲበዛብህ ትበሳጫለህ ፡፡  ይህን ጊዜ ፈገግ ብላ አልያም በአካላዊ እንቅስቃሴ ከስሜትህ ገታ እንድትል ታደርግሃለች ››ብለዋል ፡፡

ያንን ማድረግ ቀላል አይደለም ፡፡በ2004 የወንዶቹን የዩኤፋ ካፕ ማጣሪያ ጨዋታ  በመምራት ቀዳሚዋ ሴት የነበረችው ኒኮል ፔቲግናት የተለየ መንገድን ትከተል ነበር ፡፡ያንን የምታደርገው በተሳሳተ መንገድ እንዳይተረጎምብኝ በሚል ስጋት ነበር ፡፡  ‹‹ሜዳ ላይ በተቻለኝ መጠን ከተጫዋቾቹ እርቅ ነበር ›› ብላለች ኒኮል በ2008 በተደረገላት ቃለ ምልልስ ፡፡ፈገግታ በማሳየት አሊያም በሌላ መንገድ ውሳኔዬን ለማለሳለስ አልሞክርም ነበር ፡፡ ሰዎች መንታ ገጽ ያለው መልዕክት እንዳስተላለፍኩ እንዲያስቡ በሩን አልፈቅድላቸውም ነበር ››

ፍራፓርት የወንዶቹን ጨዋታ መዳኘት ከጀመረች ወዲህ በጾታዋ ምክንያት ክብር እንደተነፈገች የተሰማት በውስን አጋጣሚዎች እንደሆነ ትናገራለች፡፡ከእነዚህ መካከል ያለምንም ጥርጥር በጥቅምት 2015 የሆነው ነው ፡፡ቫሌንሲዬን ከ ላቫል ጋር ያለጎል አቻ በተለያየበት ጨዋታ የቫሌንሲዬኑ አሰልጣኝ ዴቪድ ለ ፍራፐር የፍጹም ቅጣት ምት ያለ አግባብ ተከልክለናል ሲሉ ቁጣቸው ነደደ፡፡ ‹‹ግልጽ የፍጹም ቅጣት ምት ነበር ፡፡ ነገር ግን አልቢትሯ አላየችውም ፡፡ሴት ሆነህ የወንዶችን ስፖር ለመዳኘት ስትሞክር ውስብስብ ይሆናል ›› ሲሉ ከጨዋታው በኋላ ተናገሩ ፡፡በርግጥ ከደቂቃዎች በኋላ የፈጸሙት ትልቅ ስህተት መሆኑን ተገንዝበው በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል ፡፡

ይህን በመሰለው ዘለፋ ያልተረታችው ፍራፓርት የዳኝነት ዘመኗ እያበበ ሄደ ፡፡ የሱፐር ካፑን ጨዋታ እንድትመራ መመረጧ  ደግሞ የቅርብ ጊዜ ስኬቷ ሆኗል ፡፡ ‹‹እንደሚቻል ማሳየት ትልቅ እርካታ ያጎናጽፋል ፡፡  በቴሌቪዥን መስኮት የሚመለከቱኝ ወጣት ሴቶች ያለሙትን ነገር ማሳካት እንደሚችሉ ያውቃሉ ፡፡ ተሰጥኦዋቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ያነሳሳቸዋል ብዬም አምናለሁ ›› ስትል ባለፈው ሰኔ ተናግራለች፡፡   

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *