በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ አትክልት ተራ አካባቢ አንድ የ20 ዓመት ወጣት ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መሞቱ ተገለጸ

9 Sep by EthioFM

በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ አትክልት ተራ አካባቢ አንድ የ20 ዓመት ወጣት ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መሞቱ ተገለጸ

የ20 ዓመቱ ታዳጊ ወጣት ጅብሪል አህመድ በአትክልት ተራ አካባቢ የተለያዩ አትክሎትችን በመቸርቸር ስራ ህይወቱን ይመራ እንደነበር ኢትዮ ኤፍ ኤም በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች አረጋግጧል።

እናቱን በቅርቡ በሞት በማጣቱ ምክንያት ታናናሾቹን አንድ ወንድምና እህቱን ከዚሁ ስራ በሚያገኘው ገቢም ያስተዳደር ነበር።

ይሁንና በትናንትናው ዕለት ጧት ላይ ከአንድ ሰው ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ። በሁለቱ ግገለሰቦች ምክንያት በአካባቢው የነበሩ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች እንደመጡ በወጣት ጅብሪል አህመድ ላይ ሶስት ጥይት ተኩሰው እንደገደሉት የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

ወጣት ጅብሪል ወዲያውኑ ወደ አቤት ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።

የሟች አስከሬንም ዛሬ ለአካባቢው ነዋሪዎች በመሰጠቱ ስርዓተ ቀብሩ በኮልፌ ሙስሊም መቃብር አካባቢ ተፈጽሟል።

ፖሊስ ጉዳዩን በሚገባ ሳያጣራ ጥይት መተኮሱም በተለይም በስፍራው የነበሩ ሰዎችን አስቆጥቷል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ፖሊስ ጉዳዩን ሳያጣራ ነው ልጁ ላይ የተኮሰበት፣መንግስት ጉዳዩን አጣርቶ በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በጉዳዩ ዙሪያ መልስ እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *