በአዲስ አበባ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይና 53 ሺ የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ

9 Sep by EthioFM

በአዲስ አበባ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይና 53 ሺ የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በማህበራዊ ድረገጹ እንዳስታወቀው በኮሚሽኑ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የማረጋገጥና የመከታተል ስራ በመስራትና ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት ጳጉሜ 3 ቀን 2011 ዓ/ም በተጠርጣሪዎቹ ቤት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 7 ሚሊዮን 608 ሺ የኢትዮጵያ ብር እና 53 ሺ የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦችን ከገንዘብ መቁጠሪያ ማሽን ጭምር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ሃላፊ ኮማንደር አወል አህመድ አስታውቀዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የውጪ ሃገራት ዜጎች የሚበዙባቸውን አካባቢዎች በጥናት በመለየትና ቪላ ቤቶችን በመከራየት በህገ ወጥ መንገድ የውጪ ሃገራት ገንዘቦችን የመመንዘር ተግባር እንደሚያከናውኑ የተናገሩት ኮማንደር አወል ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ደላሎችን ጨምሮ 10 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን አስታውሰው የምርመራው ውጤቱ የደረሰበትን ደረጃ በቀጣይ ለህብረተሰቡ እንደሚያሳውቁ ገልፀዋል፡፡

በድብቅ የሚከናወኑ እንዲህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራት የሃገርን ኢኮኖሚ የሚያዳክሙ እና ጤናማ የገበያ ስርአትን የሚጎዱ በመሆናቸው ህ/ሰቡ ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ኮማንደር አወል ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *