ፖሊስ በአዲስ አበባ መካኒሳ አካባቢ እንጀራን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው ሲጋግሩና ሲሸጡ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን ያዘ

የንፋስ ስልክ ፖሊስ መምሪያ ባዕድ ነገር በመቀላቀል እንጀራ እየጋገሩ ለገበያ ያቀርባሉ ያላቸውን ሁለት ግለሰቦች በህዝብ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል

ፖሊስ መምሪያ ከህዝብ የደረሰውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም በወረዳ 3 ክልል መካኒሳ አቦ ጀርባ በተከራዩት ቤት ውስጥ ባዕድ ነገር በመቀላቀል እንጀራ እየጋገሩ ለገበያ ያቀርባሉ ያላቸውን ሁለት ግለሰቦችን መያዙን አስተውቋል፡፡

የመካኒሳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መርማር ረዳት ሳጅን ስሜነህ ብድሬ እንደሳወቁት ፖሊስ ከህዝብ የመጣውን ጥቆማ ለወረዳ ንግድና እንዱስትሪ ጽህፈት ቤት እና ለምግብ መድሃኒትና ጤና እክብካቤ አስተዳደር ጽህፈት ቤት በመሳወቅ በቦታው ተገኝተው ሁኔታውን በጋራ ማጣራታቸውን አስታውቀዋል፡፡

እንጀራው በሚጋገርበት ቤት ውስጥ በ8 በርሚል የተቦካ ሊጥና ዱቄት መገኘቱን የገለጹት ረዳት ሳጅን ስሜነህ የዱቄቱ ናሙና ለሚመለከተው አካል ተልኮ ስለሚያስከተለው ጉዳት ለማረጋገጥ ምርመራ እንደሚደረግ እና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም ሁለት ተጠርጣርዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

የወረዳ 3 የምግብ መዳሃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ዕ/ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ በላይ በባኩላቸው ተጠርጣርዎቹ እንጀራውን እየጋገሩ ለገበያ የሚያቀርቡት ከጽህፈት ቤቱ የተሰጠ የብቃት ማረጋገጫና የንግድ ፍቃድ ሰይኖራቸው ነው ብለዋል፡፡

እንጀራው የሚጋገርበት ሁኔታም ንፅናውን የጠበቀ ባላመሆኑ በሂደት የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ሊፈጥር እንደሚችል የተናገሩት አቶ አሰፋ በላይ ህብረተሰቡ ተመሳሳይ ተግባራትና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያገጥሙት ለሚመለከታቸው አካላት ጥቆማ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

መረጃው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *