አውስትራሊያ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የነጻ ትምህርት እድል አቋረጠች

ለኢትዮጵያ ነፃ ትምህርት ዕድልን ከሚሰጡ ሀገራት ውስጥ ቻይና፣ ሀንጋሪ፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ኮሪያ፣ቱርክ፣ጃፓን ፣አወስትራሊያ እና ጣሊያን ቀዳሚ አገራት ናቸው፡፡

አውስትራሊያ ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ ከመጀመሪያ ድግሪ አንስቶ እስከ ሶስተኛ ድግሪ ድረስ ነጻ የትምህርት አድል ከሚሰጡ አገራት መካከል አንዷ ነበረች።

ይሁንና አሁን ላይ አገሪቱ ለኢትዮጵያዊያን የምትሰጠውን ነጻ የትምህርት እድል ማቋረጧን የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የዓለም አቀፋዊ አጋርነት እና ስኮላርሺፕ ዳይሬክተር አቶ ምትኩ በሬቻ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቁት ሀገሪቱ በየዓመቱ ከውጭ ሀገራት የሚበረከትላትን ነፃ የትምህርት ዕድል በመጠቀም ተማሪዎቿን ወደ ተለያዩ ሀገራት ብትልክም የተማሪዎች ሄዶ መቅረት ግን እድሉን እንድትከለከል እያደረጋት ነው፡፡

በምሳሌነት አውስትራሊያን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ሚኒስቴሩ በየዓመቱ ከ15 በላይ የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ነፃ የትምህርት ዕድል ለኢትዮጲያ ትሰጥ የነበረችው አውስትራሊያ ይህን ዕደል መስጠት ማቆሟን ተናግረዋል፡፡

በአውስትራሊያ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት የነፃ ትምህርት እድል ተጠቃዎች ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወደ ሀገራቸው መመለስ አለባቸው፡፡

ከአራት ዓመት በፊት በነጻ የትምህርት እድል ኮታ መሰረት ወደ አውስትራሊያ ያመሩት ተማሪዎች ግን ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አገራቸው ባለመመለሳቸው ኢትዮጲያ የምታገኘው እድል እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከአውስትራሊያ አቻው ጋር ባደረገው ስምምነት አገሪቱ በድጋሚ እድሉን መስጠት ችላ ነበር።

ይሁንና በነጻ የትምህርት እድሉ መሰረት የተላኩት ኢትዮጵያዊያን ግን በድጋሚ በመቅረታቸው አገሪቱ በቋሚነት እድሉን ለኢትዮጵያ መስጠት ማቆሟን አቶ ምትኩ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ ከሀገር ሲወጡ ውል ፈፅመው የሚሄዱ ሲሆን በውሉ መሰረት በፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ለትምህርታቸው የወጣውን ወጪ እንዲከፍሉ ማስወሰን እና መቅጣት ቢቻልም በዚህ ልክ የሄደ አካል ግን የለም ብለዋል፡፡

በትግስት ዘላለም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *