የሳውዲው ልኡል የኢራን እንቅስቃሴ ካልተገታ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ያሻቅባል አሉ

የሳውዲው ልኡል ሙሀመድ ቢን ሰልማን በሳውዲ እና በኢራን መካከል እየተካረረ የመጣው ውጥረት በአለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በሳውዲ ሁለት የነዳጅ ማምረቻ ጣቢያዎች ላይ ኢራን ፈጸመች በተባለው ጥቃት ሁለቱ ሀገራት የጎሪጥ እየተያዩ ነው፡፡

ኢራን ክሱን ብታጣጥለውም፡፡

ከሲቢኤስ ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ልኡሉ ቢን ሰልማን ከጋዜጠኛ ጀማል ካሹጊ ግድያ ጋር በተያያዘ በተወሰነ ደረጃ ሀላፊነት እወስዳለሁ ቢሉም ግድያውን ግን አላዘዝኮም ሲሉ ክደዋል፡፡

ሰልማን የአለም መንግስታት ኢራንን በጊዜ በጅ የማይሏት ከሆነ እመኑኝ የነዳጅ ዋጋ ከሚገመተው በላይ ያሻቅባል ብለዋል፡፡

በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የየመን ሁቲ አማጺያን አርማኮ የተሰኘው የሳውዲ መንግስት ንብረት በሆነ የነዳጅ አልሚ ኩባንያ ላይ ባደረሱት የድሮን ጥቃት የነዳጅ ማውጣቱና መላኩ ስራ ቀዝቅዟል።

አማጺያኑ ትናንት እንዳስታወቁት ደግሞ ሶስት ብርጌድ የሳውዲ ወታደሮችን ማርከናል ማለታቸው ይታወሳል።

ሳውዲ ስለተማረኩት ወታደሮች እስካሁን ያለችው ነገር ባይኖርም እንደ ቀለድ በየመን የጀመረችው ጦርነት ሳውዲንና ጋሻ ጃግሬዎቿን ለውርደት ዳርጓል።

በአሜሪካ ለሚጣልብኝ ተደጋጋሚ ማዕቀቦች ምክንያቷ ሳውዲ ነች የምትለው ኢራን ሁቲዎች ሳውዲን እንዲያጠቁ ድጋፏን የገፋችበት ይመስላል።

በያይኔአበባ ሻምበል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *